የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማሕበር በከያኔ ቴዲ አፍሮ ላይ እየደረሰ ባለው ጫና ላይ የሰጠው መግለጫ

የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማሕበር በሰሜን አሜሪካ ታዋቂው ከያኔ ቴዲ አፍሮ በቅርቡ በለቀቀው የሙዚቃ
አልበም ምክንያት ከመንግሥት አካላት የንብረት ዘረፋ፣ ማስፈራራትና፣ ጫና እየደረሰበት እንደሆነ
የሚያሳዩ የተለያዩ የሚዲያ ዘገባዎችን በጥልቀት እየተከታተለ ነው። ማሕበሩ ይህ ሁኔታ እጅግ
እንዳሳሰበው እየገለጸ ሙዚቃና ስነ-ጥበብ የህዝብ ድምፅ ናቸውና ከያኔዎች ሀሳባቸውን በነፃነት የማቅረብ
መብታቸው እንዲከበርላቸው ይጠይቃል።


ቴዲ አፍሮ በሙዚቃው የኢትዮጵያ ታሪክ፣ አንድነትና ባህል ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ በተለይም ለታሪክና
ቅርስ ጥበቃ እንዲሁም ለአድዋ ድል ጀግና ለአጼ ምኒሊክ ያቀረበው ጣዕመ ዜና ከኢትዮጵያም አልፎ ዓለም
ዓቀፍ ታዋቂነትን አትርፎለታል። የቴዲ አፍሮ የዘፈን ስንኞች ትውልድን ለማስተማርና ታሪካችንን
ለማስታወስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው ። ይህ አይነት ወርቃማ ጥበባዊ ስራ ለህዝብ የሚያበረክት ከያኔ
ሊከበርና ሊሸለም እንጂ ሊገፋና ሊሳደድ አይገባም።


በዚህም መሠረት ማኀበሩ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመንግስት ያቀርባል
1) የቴዲ አፍሮን ቤተሰቦች፣ ጓደኞች፣ አድማጭና አድናቂዎችን ደህንነትና ሰላም እንዲያረጋግጥ፣
2) በቴዲ አፍሮ ላይ የሚደረገውን ማስፈራትና ማዋከብ በአሰቸኳይ እንዲቆም፣
3) በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት በተረጋገጠውና አገሪቱ በፈረመቻቸው የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች
ውስጥ የተደነገጉት የፈጠራና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶች እንዲከበሩ፣
4) ቴዲ አፍሮና ሌሎች የጥበብ ሰዎች ያለ ፍርሃት፣ መሳቀቅና መሸማቀቅ ስራቸውን እንዲያከናውኑ
መንግሰት ዋስትና እንዲሰጥ።


አገራችን ኢትዮጵያ የታሪክ፣ የባህል፣ የቅርስ፣ ስነ ጥበብና ስነ ጽሁፍ ባለቤትና መናኸሪያ እንደመሆኗ
መንግሥት የከያኔዎችን የስነ ጥበብ ነፃነትን ማክበር የታሪካችንንና የባህላችንን ቀጣይነት ለማረጋገጥ
አስፈላጊ እንደሆነ አውቆ አስቸኳይ የጥበቃ እርምጃ እንዲወስድ ለማሳሰብ እንወዳለን።
የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማሕበር በሰሜን አሜሪካ
ሚያዚያ 18 ቀን 2018 ዓ.ም. (April 26, 2026)

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *