በአል ነጃሲ መስጊድ ላይ ስለደረሰው ጥቃት የተሰጠ መግለጫ

ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም. (ጃንዋሪ 15, 2021)

የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ (ኢ.ው.ቅ.ማ.ሰ.አ.) ጥር 2003 ዓ.ም. ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የቀደሙ አባቶቻችንና እናቶቻችን ያወረሱንን ታሪክ፣ ትውፊትና ቅርስ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍና ተተኪው ትውልድ በአገራችን ባሕልና ወግ እንዲታነጽ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷና አንድነቷ የተጠበቀ አንዲሁም ዜጎቿ በሰላም የሚኖሩባት አገር እንድትሆን የኢ.ው.ቅ.ማ.ሰ.አ. ጽኑ ምኞት አለው።
የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማኅበር በሰሜን አማሪካ በአል ነጃሲ መስጊድ ላይ በደረሰው ጥቃት በእጅጉ ማዘኑን ይገልጻል። የአል ነጃሲ መስጊድ ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ክርስትናን ከእስልምና ጋር ያስተሳሰረ ታሪካዊ መስጊድ ነው። ይህ ጥንታዊ መስጊድ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚኮሩበት ቅርሳቸውና ታሪካቸው ከመሆኑም በላይ ለጎብኝዎችም መስህብ ነው።

የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ በታሪካዊ ቤተ እምነቶች፣ሀወልቶች፣ቅርሶችና የተለያዩ አገር ንብረቶች ላይ ለጠባብ ፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ በተለያዩ ቡድኖችና አካላት የሚደርሰውን ጥቃት በጥብቅ ያወግዛል። ኢትዮጵያዊያን የመረጡትን ኃይማኖታቸውን በግላቸው ይዘው እርስ በርስ ተከባብረው፣ተጋብተው፣ ተጎራብተውና ተፋቅረው ለዘመናት ኖረዋል፣ አሁንም እየኖሩ ነው ለወደፊቱም ይኖራሉ።

በአል ነጃሲ መስጊድና በሌሎችም ኃይማኖታዊና ታሪካዊ ቦታዎች ላይ ጥቃት፣ውድመትና ቃጠሎ ያደረሱ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች ማንነታቸው ተጣርቶ በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማህበራችን ይጠይቃል። ለአገር ቅርሶችና ቤተ እምነቶች ጥበቃ ማድረግና ደህነነታቸውን ማረጋገጥ የመንግስት ግዴታና ኃላፊነት መሆኑን ለማስገንዘብ እንወዳለን። ካለፉት ሶስት አመታት አንስቶ የምዕመናን መጨፍጨፍና መፈናቀል እንዲሁም የቤተክርስቲያኖችና መስጊዶች ቃጠሎ፣ ውድመትና ዝርፊያ ላይ መንግስት ያሳውየን ቸልተኝነት ግዴለሽነት በጥብቅ እናወግዛለን። ህዝብ እንደ ቅጠል ሲረግፍ፣ ሲጨፈጨፍና ሲታረድ መንግስት ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዱ አንዳንድ ወገኖች “የመንግስትም እጅ አለበት” እስከማለት ደርሰዋል። ስለሆነም መንግስት ሰንካላ ምክንያቶችን መደርደሩን አቁሞ የዜጎችን ደህንነትና ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አበክረን እንጠይቃለን።

አል ነጃሺ መስጊድ በአስቸኳይ ታድሶ እንደ በፊቱ አገልግሎቱን እንዲቀጥል መንግስት በአስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ በጥብቅ እንጠይቃለን። እያንዳንዱም ዜጋ ለቅርሶችና ቤተ እምነቶች መጠበቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባውም እናሳስባለን።የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማኅበር በሰሜን አማሪካን ለመስጊዱ እድሳት አቅማችን በሚፈቀደው መንገድ ለመተባበር ዝግጁ መሆናችንንም ለማሳወቅ እንወዳለን።

ኢትዮጵያ በአንድነቷና በሉዓላዊነቷ ጸንታ ለዘላለም ትኑር!

የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማኅበር በሰሜን አማሪካ

 

president@ehsna.org
Secretary@ehsna.org
pr@ehsna.org
1317 Orren Street NE, Washington DC 2002

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *